ሐዋርያት ሥራ 8:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ሳውልም በእስጢፋኖስ መገደል ተስማምቶ ነበር።በዚያ ቀን በኢየሩሳሌም በነበረችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ተነሣ፤ ከሐዋርያትም በስተቀር አማኞች በሙሉ በይሁዳና በሰማርያ አውራጃዎች ሁሉ ተበተኑ፤

2. በመንፈሳዊ ነገር የተጉ ሰዎችም እስጢፋኖስን ቀበሩት፤ ደግሞም እጅግ አለቀሱለት።

3. ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ታጥቆ ተነሣ፤ ከቤት ወደ ቤት በመግባትም ወንዶችንና ሴቶችን ጐትቶ እያወጣ ወህኒ ቤት ያስገባቸው ነበር።

4. የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ፤

5. ፊልጶስም ወደ አንዲት የሰማርያ ከተማ ወርዶ ክርስቶስን ሰበከላቸው።

6. ብዙ ሕዝብም ፊልጶስ የተናገረውን ሲሰሙና ያደረገውንም ታምራዊ ምልክቶች ሲያዩ፣ አንድ ልብ ሆነው ያዳምጡት ነበር።

7. ርኵሳን መናፍስትም እየጮኹ ከብዙ ሰዎች ወጡ፤ ብዙ ሽባዎችና አንካሶችም ተፈወሱ፤

8. ከዚህ የተነሣም በከተማዪቱ ታላቅ ደስታ ሆነ።

9. ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲል በከተማዪቱ ውስጥ እየጠነቈለ የሰማርያን ሰዎች ሁሉ ያስገረመ፣ ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ራሱን እንደ ታላቅ ሰው ይቈጥር ነበር።

10. ከታናሽ እስከ ታላቅ ያለው ሰው ሁሉ፣ “ይህ ሰው ‘ታላቁ ኀይል’ በመባል የሚታወቀው መለኮታዊ ኀይል ነው” በማለት ከልብ ያዳምጡት ነበር፤

11. ከብዙ ጊዜ ጀምሮ በጥንቈላ ሥራው ስላስገረማቸውም ትኵረት ሰጥተው ይከተሉት ነበር።

ሐዋርያት ሥራ 8