11. እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤
12. መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቃቸው ነበር፤ ርኵሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር።
13. እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኵሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤
14. የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር።
15. ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው።
16. ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቁታቸውን ሸሹ።
17. ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ።
18. ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ ተናዘዙ፤
19. ሲጠነቁሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ አምሳ ሺህ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ።
20. በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
21. ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ።
22. ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ።
23. በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ።
24. ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም።
25. እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ።
26. ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና።
27. የዚህ የሥራችን መልካም ስም ከመጒደፉም በላይ፣ መላው እስያና ዓለም የሚያመልካት የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስም ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ደግሞም ገናናው ክብሯ ይዋረዳል።”
28. ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጥተው፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር።
29. ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋር ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ።
30. ጳውሎስም ወጥቶ ሕዝቡ ፊት ለመቅረብ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከለከሉት።