ሐዋርያት ሥራ 13:17-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብፅ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው።

18. አርባ ዓመት ያህልም በበረሓ ታገሣቸው፤

19. በከነዓን ምድር የነበሩትንም ሰባት መንግሥታት አጥፍቶ፣ ምድራቸውን ለገዛ ሕዝቡ ርስት አድርጎ አወረሳቸው።

20. ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር።“ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።

21. ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው።

22. ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ስለ እርሱም፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት።

23. እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ።

24. ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር።

25. ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ እንኳ መፍታት የማይገባ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር።

26. “እናንት ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው።

27. የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በእርሱ ፈረዱበት።

28. ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት።

ሐዋርያት ሥራ 13