ሐዋርያት ሥራ 13:15-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ፣ የምኵራብ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሕዝቡን የሚመክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ሲሉ ላኩባቸው።

16. ጳውሎስም ተነሥቶ በእጁ በመጥቀስ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ደግሞም እናንት እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ አድምጡ።

17. የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብፅ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው።

18. አርባ ዓመት ያህልም በበረሓ ታገሣቸው፤

19. በከነዓን ምድር የነበሩትንም ሰባት መንግሥታት አጥፍቶ፣ ምድራቸውን ለገዛ ሕዝቡ ርስት አድርጎ አወረሳቸው።

20. ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር።“ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው።

21. ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው።

22. ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ስለ እርሱም፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት።

23. እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ።

24. ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር።

25. ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ እንኳ መፍታት የማይገባ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር።

ሐዋርያት ሥራ 13