2 ዜና መዋዕል 34:9-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር።

10. እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እየተቈጣጠሩ እንዲያሠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ።

11. እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለዐናጢዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ።

12. ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣

13. የጒልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።

14. ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።

15. ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።

16. ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤

17. በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”

18. ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።

19. ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።

20. እርሱም ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም፣ ለሚክያስ ልጅ ለዓብዶን፣ ለጸሓፊው ለሳፋንና ለንጉሡ የቅርብ አገልጋይ ለዓሳያ ይህን ትእዛዝ ሰጠ፤

21. “ሄዳችሁ ስለ እኔ እንደዚሁም በእስራኤልና በይሁዳ ስላሉት ቅሬታዎች በተገኘው መጽሓፍ ውስጥ ስለ ተጻፈው ነገር እግዚአብሔርን ጠይቁ። አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ በላያችን ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቊጣ ፈስሶአል፤ በዚህ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት አልተመላለሱምና።”

22. ኬልቅያስና ንጉሡ ከእርሱ ጋር የላካቸው ሰዎች የአልባሳት ጠባቂ የነበረው የሐስራ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የሴሌም ሚስት ወደሆነችው ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄደው ነገሯት። እርሷም በኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ክፍለ ከተማ ትኖር ነበር።

23. ነቢይቱም እንዲህ አለቻቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤

24. ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ በተጻፈው ርግማን ሁሉ መሠረት፣ በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ ጥፋትን አመጣለሁ።

25. እኔን ትተውኝ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑና እጃቸው በሠራው ነገር ሁሉ ለቊጣ ስላነሣሡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ስፍራ ይነድ ዳል፤ አይጠፋምም።’

26. እግዚአብሔርን ለመጠየቅ የላካችሁን የይሁዳን ንጉሥ እንዲህ በሉት፤ ‘ስለ ሰማኸው ቃል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

27. በዚህ ስፍራና በሕዝቡ ላይ የተናገረውን በሰማህ ጊዜ፣ ልብህ ስለ ተነካና በእግዚአብሔርም ፊት ራስህን ስለአዋረድህ፣ እንዲሁም በእኔ ፊት ራስህን ዝቅ ስላደረግህ፣ ልብስህንም በመቅደድ በፊቴ ስለአለቀስህ፣ ሰምቼሃለሁ ይላል እግዚአብሔር።

28. እነሆ፤ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ትቀበራለህ፤ በዚህ ቦታና በነዋሪዎቹ ላይ የማመጣውን መከራ ሁሉ በዓይንህ አታይም።’ ” መልሷንም ይዘው ወደ ንጉሡ ሄዱ።

2 ዜና መዋዕል 34