3. መንግሥቱን ካጸና በኋላ፣ ንጉሥ የነበረውን አባቱን የገደሉትን ሹማምት በሞት ቀጣቸው።
4. እግዚአብሔር በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው ሕግ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች ስለ ልጆቻቸው አይገደሉ፤ ልጆችም ስለ ወላጆቻቸው አይገደሉ” ብሎ ባዘዘው መሠረት አደረገ እንጂ ልጆቻቸውን አልገደለም።
5. አሜስያስ የይሁዳን ሕዝብ በአንድነት ሰብስቦ፣ እንደየቤተ ሰቡ በሻለቆችና በመቶ አለቆች በመደልደል በመላው ይሁዳና በብንያም መደባቸው። ከዚያም ዕድሜያቸው ሃያና ከሃያ በላይ የሆናቸውን ሰብስቦ፣ ለውትድርና አገልግሎት ብቁ ሆነው ጋሻና ጦር መያዝ የሚችሉ ሦስት መቶ ሺህ ሰዎች አገኘ።
6. እንዲሁም በመቶ መክሊት ጥሬ ብር አንድ መቶ ሺህ ተዋጊዎች ከእስራኤል ቀጠረ።
7. ነገር ግን አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እርሱ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤልም ሆነ ከማናቸውም የኤፍሬም ሕዝብ ጋር አይደለምና፣ እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ከአንተ ጋር አይዝመቱ።
8. ሄደህ ጦርነቱን በቈራጥነት ብትዋጋም እንኳ፣ የመርዳትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ሆነ እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል።”
9. አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፣ “ታዲያ ለእነዚህ ለእስራኤል ወታደሮች የከፈልኩት መቶ መክሊት እንዴት ይሁን?” ሲል ጠየቀው የእግዚአብሔርም ሰው፣ “እግዚአብሔር ከዚህ አብልጦ ሊሰጥህ ይችላል” ሲል መለሰለት።
10. ስለዚህ አሜስያስ ከኤፍሬም ወደ እርሱ የመጡትን ወታደሮች ወደየመኖሪያ ስፍራቸው አሰናበታቸው። እነርሱም በይሁዳ ላይ ክፉኛ ተበሳጭተው ነበርና በታላቅ ቊጣ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው ተመለሱ።
11. አሜስያስም ኃይሉን በሚገባ አደራጅቶ ሰራዊቱን ወደ ጨው ሸለቆ መራ፤ በዚያም ዐሥር ሺህ የሴይር ወታደሮችን ገደለ።
12. የይሁዳ ሰራዊት ሌሎች ዐሥር ሺህ ሰዎች ማረኩ፤ ወደ አንድ ዓለት ዐናት ላይም አውጥተው ቍልቍል ለቀቁአቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ።
13. በዚያኑ ጊዜ አሜስያስ ያሰናበታቸውና በጦርነቱ እንዳይካፈሉ የከለከላቸው ወታደሮች፤ ከሰማርያ እስከ ቤትሖሮን ያሉትን የይሁዳ ከተሞች ወረሩ፤ ሦስት ሺህ ሰው ገደሉ፤ እጅግ ብዙ ምርኮም ወሰዱ።
14. አሜስያስም ኤዶማያውያንን ደምስሶ በተመለሰ ጊዜ፣ የሴይርን ሕዝብ አማልክት ይዞ መጣ፤ ለራሱም አማልክት አድርጎ በማቆም ሰገደላቸው፤ መሥዋዕትም አቀረበላቸው።
15. የእግዚአብሔርም ቊጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።
16. እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመነሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው።ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንደወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።
17. የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “እስቲ ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።
18. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ ግን፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ‘ሚስት እንድትሆነው ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠው’ ሲል ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከበት። ከዚያም የዱር አውሬ ከሊባኖስ ወጥቶ ኵርንችቱን ረገጠው።