27. እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
28. ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ።
29. እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው።
30. አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።
31. ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀሞጦ ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።
32. እርሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።
33. ያም ሆኖ ግን ማምለኪያ ኰረብታዎች ሙሉ በሙሉ አልተወገዱም፤ ሕዝቡም ገና ልቡን በአባቶቹ አምላክ ላይ አልጣለም ነበር።
34. በኢዮሣፍጥ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያ እስከ፣ መጨረሻ የተከናወኑት ሌሎች ተግባራት የአናኒ ልጅ ኢዩ በዘገበው የእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦአል።
35. ከዚህ በኋላ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ሥራው እጅግ ክፉ ከሆነው ከእስራኤል ንጉሥ ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል አደረገ፤
36. የንግድ መርከብ ለመሥራትም ተስማሙ፤ መርከቦቹንም በዔጽዮንጋብር አሠሩ።
37. የመሪሳ ሰው የሆነው የዶዳያ ልጅ አልዓዛር በኢዮሣፍጥ ላይ፣ “ከአካዝያስ ጋር የስምምነት ውል ስለ አደረግህ፣ እግዚአብሔር ሥራህን ያፈርሰዋል” ሲል ትንቢት ተናገረበት፤ መርከቦቹም ተሰበሩ፤ ለንግዱም ሥራ መንቀሳቀስ አልቻሉም።