2 ነገሥት 5:2-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. አደጋ ጣዮች ከሶርያ ወጥተው፣ ከእስራኤል ምድር አንዲት ልጃገረድ ማረኩ፤ እርሷም የንዕማንን ሚስት ታገለግላት ነበር።

3. እመቤቷንም፣ “ጌታዬ በሰማርያ ያለውን ነቢይ ሄዶ ቢያገኘው እኮ ከዚህ ለምጹ ይፈውሰው ነበር” አለቻት።

4. ንዕማንም ወደ ጌታው ሄዶ ከእስራኤል የመጣችው ልጃገረድ ያለችውን ነገረው።

5. የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ።

6. ለእስራኤልም ንጉሥ የያዘው ደብዳቤ፣ “ከለምጹ እንድትፈውሰው ይህን ደብዳቤ አስይዤ አገልጋዬን ንዕማንን ወዳንተ ልኬዋለሁ” የሚል ነው።

7. የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀዶ፣ “ለምጽ እንድ ፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ።

8. የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ፣ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ሰውየው ወደ እኔ ይምጣ፤ ከዚያም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል።”

9. ስለዚህ ንዕማን በፈረሶቹና በሠረገሎቹ ሆኖ በኤልሳዕ ቤት ደጃፍ ሲደርስ ቆመ።

10. ኤልሳዕም፣ “ሂድና በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህ ይፈወሳል፤ አንተም ትነጻለህ” ብሎ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከበት።

11. ንዕማን ግን ተቈጥቶ እንዲህ በማለት ሄደ፤ ‘እኔ እኮ በርግጥ ወደ እኔ መጥቶ በመቆም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ በእጁም ዳሶ ከለምጽ በሽታዬ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።

12. ለዚህ ለዚህ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋር ከየትኞቹም የእስራኤል ውሆች አይሻሉምን? ለመታጠብ ለመታጠብማ በእነርሱ ታጥቤ መንጻት አልችልምን?” ስለዚህ በቍጣ ተመለሰ።

13. የንዕማን አገልጋዮች ግን ወደ እርሱ ቀርበው፣ “አባት ሆይ፤ ነቢዩ ከዚህ ከበድ ያለ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበርን? ታዲያ፣ ‘ታጠብና ንጻ’ ቢልህ ምኑ አስቸገረህ?” አሉት።

14. ስለዚህ ንዕማን ወረደ፤ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገረውም በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤ ነጻም።

2 ነገሥት 5