1. የነቢያት ማኅበር ወገን ከሆነው የአንደኛው ሚስት፣ “አገልጋይህ ባሌ ሞቶአል፤ እርሱም እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ ነበር አንተ ታውቃለህ፤ አሁን ግን ባለ ዕዳ ሁለት ወንዶች ልጆቼን ባሪያ አድርጎ ሊወስዳቸው መጥቶአል” ስትል ወደ ኤልሳዕ ጮኸች።
2. ኤልሳዕም፣ “ታዲያ እኔ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ? በቤትሽ ምን እንዳለ ንገሪኝ” አላት።እርሷም፣ “አገልጋይህ ከጥቂት ዘይት በቀር በቤቷ ምንም ነገር የላትም” አለች።
3. ኤልሳዕም እንዲህ አላት፤ “እንግዲያው ሂጂና ከጎረቤቶችሽ ሁሉ ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ፤
4. ገብተሽም መዝጊያውን ባንቺና በልጆችሽ ላይ የኋሊት ዝጊው፤ ዘይቱንም በማድጋዎቹ ሁሉ ጨምሪ፤ እያንዳንዱ ማድጋ ሲሞላም ወደ አንድ በኩል አኑሪው።”
5. ስለዚህ ትታው ሄዳ መዝጊያውን በራሷና በልጆቿ ላይ የኋሊት ዘጋችው። ማድጎቹን እያቀረቡላትም እርሷ ትሞላ ጀመር።
6. ማድጋዎቹ ሁሉ ከሞሉ በኋላ ልጇን፣ “ሌላ ማድጋ አምጣ” አለችው።እርሱ ግን፣ “ምንም የቀረ ማድጋ የለም” ሲል መለሰላት። ከዚያም ዘይቱ መውረዱን አቆመ።
7. እርሷም ሄዳ ይህንኑ ለእግዚአብሔር ሰው ነገረችው። እርሱም፣ “ሄደሽ ዘይቱን በመሸጥ ዕዳሽን ክፈይ፤ የተረፈውም ለአንቺና ለልጆችሽ መተዳደሪያ ይሁን” አላት።
8. አንድ ቀን ኤልሳዕ ወደ ሱነም ሄደ። በዚያም አንዲት ሀብታም ሴት ነበረች፤ እርስዋም ምግብ እንዲበላ አጥብቃ ለመነችው፤ በዚያም ባለፈ ቍጥር ምግብ ለመብላት ወደ ቤቷ ይገባ ነበር።