2 ቆሮንቶስ 11:26-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ብዙ ጊዜ በጒዞ ተንከራትቻለሁ፤ ደግሞም ለወንዝ ሙላት አደጋ፣ ለወንበዴዎች አደጋ፣ ለገዛ ወገኖቼ አደጋ፣ ለአሕዛብ አደጋ፣ ለከተማ አደጋ፣ ለገጠር አደጋ፣ ለባሕር አደጋ እንዲሁም ለሐሰተኞች ወንድሞች አደጋ ተጋልጬ ነበር።

27. ብዙ ጥሬአለሁ፤ ብዙ ደክሜአለሁ፤ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ አጥቻለሁ፤ ተርቤአለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ጊዜ ምግብ ሳልቀምስ ኖሬአለሁ፤ በብርድና በራቍትነት ተቈራምጃለሁ።

28. ሌላውን ነገር ሳልቈጥር፣ ዕለት ዕለት የሚያስጨንቀኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ሐሳብ ነው።

29. ደካማ ማን ነው? እኔስ አብሬ አልደክምምን? በኀጢአት የሚሰናከል ማን ነው? እኔስ አልቈጭምን?

30. መመካት ካለብኝ፣ ደካማነቴን በሚያሳዩ ነገሮች እመካለሁ።

31. ለዘላለም የተመሰገነው የጌታ የኢየሱስ አምላክና አባት እንደማልዋሽ ያውቃል።

32. ደማስቆ ሳለሁ ከንጉሥ አርስጦስዮስ በታች የሆነው ገዥ ሊያሲዘኝ ፈልጎ፣ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር።

33. ነገር ግን በግንቡ መስኮት በኩል በቅርጫት አውርደውኝ ከእጁ አመለጥሁ።

2 ቆሮንቶስ 11