1. ዳዊት አብሮት የነበረውን ሕዝብ ቈጠረ፤ የሻለቆችንና የመቶ አለቆችን ሾመላቸው።
2. ዳዊትም ሰራዊቱን ሲሦውን በኢዮአብ፣ ሲሦውን በኢዮአብ ወንድም በጽሩያ ልጅ በአቢሳ፣ ሲሦውን ደግሞ በጌታዊው በኢታይ አዛዥነት ሥር ላካቸው። ንጉሡም ለሰራዊቱ፣ “እኔ ራሴም አብሬአችሁ በእርግጥ እወጣለሁ” አላቸው።
3. ሰዎቹ ግን፣ “አንተ መውጣት የለብህም፤ እንድንሸሽ ብንገደድ፣ ሰዎቹ ከቁም ነገር አይቈጥሩንም፤ ግማሾቻችን እንኳ ብንሞት ደንታቸው አይደለም፣ አንተ ግን ብቻህን ከእኛ ከዐሥሩ ሺህ ትበልጣለህ፤ ስለዚህ በከተማ ሆነህ ብትረዳን ይሻላል” አሉት።
4. ንጉሡም፣ “መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ አደርጋለሁ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ በመቶና በሺህ እየሆነ ተሰልፎ ሲወጣ፣ ንጉሡ በቅጥሩ በር ቆሞ ነበር።
5. ንጉሡም ኢዮአብን፣ አቢሳንና ኢታይን፣ “ለእኔ ስትሉ በወጣቱ ልጄ በአቤሴሎም ላይ ጒዳት እንዳታደርሱበት” ብሎ አዘዛቸው። ንጉሡ ልጁን አቤሴሎምን አስመልክቶ ለእያንዳንዱ አዛዥ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰራዊቱ ሁሉ ሰማ።
6. ሰራዊቱ እስራኤልን ለመውጋት ተሰልፎ ወደ ሜዳ ወጣ፤ ጦርነቱም በኤፍሬም ደን ውስጥ ሆነ።
7. እዚያም የእስራኤል ሰራዊት በዳዊት ሰዎች ተመታ፤ በዚያም ቀን ታላቅ እልቂት ሆነ፤ ሃያ ሺህም ሰው ተገደለ።