4. ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቍረጥ መልሶ ሰደዳቸው።
5. ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
6. አሞናውያን፣ ዳዊት እንደ ጠላቸው ባወቁ ጊዜ፣ ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺህ ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን እንዲሁም ንጉሥ መዓካን ከአንድ ሺህ ሰዎቹ ጋር ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ።
7. ዳዊት ይህን ሲሰማ፣ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሰራዊት ጋር ላከው።
8. አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን እንዲሁም የጦብና የመዓካ ሰዎች ለብቻ ሜዳው ላይ ተሰለፉ።
9. ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው።
10. የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ግንባር አሰለፋቸው።
11. ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ ሶርያውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ።
12. እንግዲህ በርታ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ።
13. ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ።
14. ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
15. ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ እንደ ገና ተሰባሰቡ።
16. አድርአዛር መልክተኞችን ሰዶ ከወንዙ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጣ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ኤላም ሄዱ።
17. ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ። ሶርያውያንም ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን በግንባር ገጠሙት፤