1. ሳኦል ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ከተመለሰ በኋላ፣ “እነሆ፤ ዳዊት በዓይንጋዲ ምድረ በዳ አለ” ብለው ነገሩት።
2. ስለዚህ ሳኦል ከመላው እስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ዳዊትንና ሰዎቹን ለመፈለግ “የሜዳ ፍየሎች ዐለት” ወደተባለው ቦታ አቅራቢያ ሄደ።
3. ሳኦልም በመንገድ ዳር ወዳለው ወደ አንድ የበጎች ማደሪያ በደረሰ ጊዜ፣ ዋሻ አግኝቶ ወገቡን ሊሞክር ወደዚያ ገባ። ዳዊትና ሰዎቹም ከዋሻው በውስጠኛው ቦታ ተቀምጠው ነበር።
4. የዳዊት ሰዎችም ዳዊትን፣ “እግዚአብሔር፣ ‘የወደድኸውን ታደርግበት ዘንድ ጠላትህን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ’ ብሎ ለአንተ የተናገረው ቀን ዛሬ ነው” አሉት። ዳዊትም በልቡ እየተሳበ ሄዶ የሳኦልን ልብስ ጫፍ ማንም ሳያውቅ ቈርጦ ወሰደ።
5. ዳዊት የሳኦልን ልብስ ጫፍ በመቊረጡ ልቡ በሐዘን ተመታ።
6. ለሰዎቹም፣ “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ከማድረግና እግዚአብሔር የቀባው ስለ ሆነም እጄን በእርሱ ላይ ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ” አላቸው።
7. ዳዊት ሰዎቹን በዚህ ቃል ገሠጻቸው፤ በሳኦል ላይ አደጋ እንዲያደርሱበትም አልፈቀደላቸውም። ሳኦልም ከዋሻው ወጥቶ ሄደ።
8. ከዚያም ዳዊት ከዋሻው ወጥቶ ሳኦልን፣ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ!” ብሎ ጠራው። ሳኦልም ወደ ኋላው ዞር ባለ ጊዜ፣ ዳዊት ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ እጅ ሲነሣው ተመለከተ፤
9. ዳዊትም ሳኦልን እንዲህ አለው፤ “ሰዎች፣ ‘እነሆ፤ ዳዊት ክፉ ነገር ሊያደርግብህ ይፈልጋል’ ሲሉ ለምን ትቀበላቸዋለህ?