5. ሳኦልም ወደ አማሌቅ ከተማ ሄዶ በአንዲት ሸለቆ ውስጥ አደፈጠ።
6. እርሱም፣ ቄናውያንን፣ “ከእነርሱ ጋር እንዳላጠፋችሁ ከአማሌቃውያን ራቁ፤ ተለዩአቸውም፤ እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡ ጊዜ፣ ቸርነት አድርጋችሁላቸዋልና” አላቸው። ስለዚህ ቄናውያን ከአማሌቃውያን ተለዩ።
7. ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን ከኤውላጥ አንሥቶ በምሥራቅ ግብፅ እስካለው እስከ ሱር ድረስ ወጋቸው።
8. የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ከነሕይወቱ ማረከው፤ ሕዝቡን ሁሉ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋቸው።
9. ነገር ግን ሳኦልና ሰራዊቱ አጋግን፣ ምርጥ ምርጡን በግና የቀንድ ከብት፣ የሰባውን ጥጃና ጠቦት፣ መልካም የሆነውን ሁሉ ሳይገድሉ ተውት። እነዚህን ፈጽመው ለማጥፋት ፈቃደኞች አልነበሩም፤ ነገር ግን የተናቀውንና የማይጠቅመውን ሁሉ አጠፉ።
10. ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፤
11. “ሳኦልን በማንገሤ ተጸጽቻለሁ፤ እኔን ከመከተል ተመልሶአልና፣ ትእዛዜንም አልፈጸመምና።” ሳሙኤልም እጅግ ተጨንቆ፣ ሌሊቱን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
12. ሳሙኤልም ጠዋት ተነሥቶ በማለዳ ሳኦልን ለመገናኘት ሄደ፤ ነገር ግን፣ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ ሄዶአል፤ ለራሱ ክብር የመታሰቢያ ሐውልት በዚያ ካቆመ በኋላ ተመልሶ ወደ ጌልገላ ወርዶአል” ተብሎ ተነገረው።
13. ሳሙኤል ባገኘው ጊዜ ሳኦል፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ” አለው።
14. ሳሙኤል ግን፣ “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎች ጩኸትና የበሬዎች ግሣት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
15. ሳኦልም፣ “ሰራዊቱ ከአማሌቃውያን ማርከው ያመጧቸው ናቸው፤ ምርጥ ምርጦቹ በጎችና በሬዎች ለእግዚአብሔር ለአምላክህ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳይገድሉ የተዉአቸው ናቸው፤ የቀሩትን ግን በሙሉ አጥፍተናል” ብሎ መለሰ።