1 ሳሙኤል 15:24-35 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ።

25. አሁንም፣ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።”

26. ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።

27. ሳሙኤል ለመሄድ ዘወር ባለ ጊዜ፣ ሳኦል የልብሱን ጫፍ ያዘ፤ ተቀደደም።

28. ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጥቶታል።

29. የእስራኤል ክብር የሆነው እግዚአብሔር አይዋሽም፤ አይጸጸትምም፤ እርሱ ይጸጸት ዘንድ ሰው አይደለምና።”

30. ሳኦልም መልሶ፣ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ ነገር ግን በሕዝቤ አለቆች ፊትና በእስራኤል ፊት አክብረኝ፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ እባክህ አብረኸኝ ተመለስ” አለው።

31. ስለዚህ ሳሙኤል አብሮት ተመለሰ፤ ሳኦልም ለእግዚአብሔር ሰገደ።

32. ከዚያም ሳሙኤል፣ “የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ።አጋግም፣ “በውኑ ሞት እንዲህ መራራ ነውን? በማለት እየተንቀጠቀጠ መጣ።

33. ሳሙኤልም፣“ሰይፍህ ሴቶችን ልጅ አልባ እንዳደረገቻቸው፣እናትህም በሴቶች መካከል ልጅ አልባ ትሆናለች”ሲል አጋግን ጌልገላ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቈራረጠው።

34. ከዚያም ሳሙኤል ወደ አርማቴም ሄደ። ሳኦል ግን ወደ ቤቱ ወደ ሳኦል ጊብዓ ወጣ።

35. ሳሙኤል ለሳኦል ቢያለቅስለትም እንኳ እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ ዳግመኛ ሊያየው አልሄደም፤ እግዚአብሔርም ሳኦልን በእስራኤል ላይ በማንገሡ ተጸጸተ።

1 ሳሙኤል 15