6. እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየቊጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጒድጓዱ ሁሉ ተደበቁ።
7. ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ።ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ አብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር።
8. እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ።
9. በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።
10. ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም ሊቀበለው ወጣ።
11. ሳሙኤልም፣ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ሰራዊቱ መበታተኑን፣ አንተም በቀጠርኸው ጊዜ አለመምጣትህን፣ ፍልስጥኤማውያንም በማክማስ መሰብሰባቸውን አየሁ፤
12. ‘ስለዚህ ፍልስጥኤማውያን ወርደው ወደ ጌልገላ ይመጡብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም’ ብዬ አሰብሁ። ስለዚህ የሚቃጠል መሥዋዕት ማቅረብ ግድ ሆነብኝ።”
13. ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤
14. አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠ በቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።”
15. ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።
16. ፍልስጥኤማውያን በማክማስ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ ሳኦል፣ ልጁ ዮናታንና አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ነበሩ።
17. በሦስት ምድብ የተከፈሉ ወራሪዎች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጡ፤ አንዱ ምድብ በሦጋል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቀና፤
18. ሌላው ወደ ቤትሖሮን፣ ሦስተኛው ደግሞ በምድረ በዳው ትይዩ ካለው ከስቦይም ሸለቆ ቍልቍል ወደሚያሳየው ድንበር ዞረ።
19. ፍልስጥኤማውያን፣ “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር ለራሳቸው አይሥሩ” ብለው ስለ ነበር፣ በመላው የእስራኤል ምድር ብረት ቀጥቃጭ አልተገኘም።