1. የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋዮች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ፤ከቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በፊልጵስዩስ ላሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ቅዱሳን ለሆኑ ሁሉ፤
2. ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3. እናንተን ባስታወስሁ ቍጥር አምላኬን አመሰግናለሁ።
4. ዘወትር ስለ ሁላችሁ ስጸልይ፣ በደስታ እጸልያለሁ፤
5. ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ እስካሁን ድረስ በወንጌል አገልግሎት ተካፋይ ሆናችኋልና።
6. በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ።
7. በልቤ ስላላችሁ፣ ስለ ሁላችሁ እንዲህ ማሰቤ ተገቢ ነው፤ በእስራቴም ሆነ ለወንጌል ስመክትና ሳጸናው ሁላችሁም ከእኔ ጋር የእግዚአብሔር ጸጋ ተካፋዮች ናችሁና።
8. በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁንም ምን ያህል እንደምናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው።
9. ፍቅራችሁ በጥልቅ እውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ።