ገላትያ 4:8-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እግዚአብሔርን ከማወቃችሁ በፊት፣ በባሕርያቸው አማልክት ላልሆኑት ባሪያዎች ነበራችሁ፤

9. አሁን ግን እግዚአብሔርን ዐውቃችሁታል፤ ይልቁን ደግሞ በእግዚአብሔር ታውቃችኋል። ታዲያ እንደ ገና ወደ ደካማና ወደማይጠቅም ትምህርት እንዴት ትመለሳላችሁ? ዳግም በእርሱ በባርነት ለመጠመድ ትፈልጋላችሁን?

10. ልዩ የሆኑ ቀኖችን፣ ወሮችን፣ ወቅቶችንና ዓመታትን ታከብራላችሁ።

11. ስለ እናንተ በከንቱ የደከምሁ እየመሰለኝ እፈራላችኋለሁ።

12. ወንድሞች ሆይ፤ እለምናችኋለሁ፤ እኔ እናንተን እንደ መሰልሁ እናንተም እኔን ምሰሉ። እናንተ አንዳች አልበደላችሁኝም።

13. እንደምታውቁት በመጀመሪያ ለእናንተ ወንጌልን የሰበክሁት፣ በሕመም ምክንያት ነበር።

14. ሕመሜ ለእናንተ ፈተና ሆኖባችሁም እንኳ፣ አልሰለቻችሁኝም፤ ወይም አልተጸየፋችሁኝም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ፣ እንዲያውም እንደ ራሱ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አድርጋችሁ ተቀበላችሁኝ።

15. ለመሆኑ ያ ሁሉ ደስታችሁ የት ደረሰ? ቢቻላችሁ ዐይናችሁን ቢሆን እንኳ አውጥታችሁ የምትሰጡኝ እንደ ነበራችሁ እመሰክራለሁ።

16. እውነቱን ስለ ነገርኋችሁ ጠላት ሆንሁባችሁን?

17. እነዚያ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሊወስዷችሁ ይተጋሉ፤ ለበጎ ግን አይደለም፤ የሚፈልጉት እናንተን ከእኛ ነጥለው የራሳቸው ሊያደርጓችሁ ነው።

ገላትያ 4