ዳንኤል 6:14-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ።

15. ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት።

16. ስለዚህ ንጉሡ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም ዳንኤልን አመጡት፤ ወደ አንበሶችም ጒድጓድ ጣሉት። ንጉሡም ዳንኤልን፣ “ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ያድንህ” አለው።

17. ድንጋይ አምጥተው በጒድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም፣ በዳንኤል ላይ የተፈጸመው እንዳይለወጥ በራሱ የቀለበት ማኅተምና በመሳፍንቱ ቀለበቶች አተመበት።

18. ንጉሡም ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ፤ በዚያም ሌሊት ምግብ ሳይበላ፣ የሚያዝናናውም ነገር ሳይቀርብለት ዐደረ፤ እንቅልፍም ከእርሱ ራቀ።

19. በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ፤ ንጉሡ ተነሥቶ ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ እየተጣደፈ ሄደ።

20. ወደ ጒድጓዱም ቀርቦ በሐዘን ድምፅ ዳንኤልን፣ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ፤ ሁል ጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ።

ዳንኤል 6