6. ነገር ግን ሕልሙንና ትርጒሙን ብትነግሩኝ፣ ስጦታና ሽልማት፣ ታላቅ ክብርም ከእኔ ትቀበላላችሁ፤ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጒሙንም አሳውቁኝ።”
7. እነርሱም እንደ ገና፣ “ንጉሥ ሕልሙን ለአገልጋዮቹ ይንገረን፤ እኛም እንተረጒመዋለን” ብለው መለሱ።
8. ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቼአለሁ፤
9. ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጒሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።”
10. ኮከብ ቈጣሪዎቹም ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር ላይ አይገኝም! ማንም ንጉሥ ምንም ያህል ታላቅና ኀያል ቢሆን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ማንኛውንም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ኮከብ ቈጣሪን ጠይቆ ዐያውቅም።
11. ንጉሡ የሚጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት ከአማልክት በቀር ለንጉሡ የሚገልጽለት የለም።”
12. ይህም ንጉሡን እጅግ አበሳጨው፤ አስቈጣውም፤ በባቢሎን ያሉ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ፤