ዳንኤል 2:19-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

19. ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ፤

20. እንዲህም አለ፤“ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ።

21. ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ደግሞም ያወርዳቸዋል፤ጥበብን ለጠቢባን፣ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።

22. የጠለቀውንና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤በጨለማ ያለውን ያውቃል፤ብርሃንም ከእርሱ ጋር ይኖራል።

23. የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤አከብርሃለሁም፤ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።”

24. ዳንኤልም የባቢሎንን ጠቢባን እንዲገድል ንጉሡ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ሄዶ፣ “የባቢሎንን ጠቢባን አትግደል፤ ወደ ንጉሡ ውሰደኝ፤ እኔም ሕልሙን እተረጒምለታለሁ” አለው።

25. አርዮክም ዳንኤልን ወዲያውኑ ወደ ንጉሡ በመውሰድ፣ “ሕልሙንና ትርጒሙን ለንጉሡ መግለጥ የሚችል ሰው ከይሁዳ ምርኮኞች መካከል አግኝቻለሁ” አለው።

26. ንጉሡም ብልጣሶር የተባለውን ዳንኤልን፣ “ያየሁትን ሕልምና ትርጒሙን ልትነግረኝ ትችላለህን?” አለው።

27. ዳንኤልም እንዲህ አለ፤ “አንድም ጠቢብ፣ አስማተኛ፣ ጠንቋይም ሆነ ቃላተኛ ንጉሡ የጠየቀውን ምስጢር መግለጥ የሚችል የለም፤

28. ነገር ግን ምስጢርን የሚገልጥ አምላክ በሰማይ አለ፤ እርሱም በሚመጡት ዘመናት የሚሆነውን ነገር ለንጉሥ ናቡከደነፆር ገልጦአል፤ በዐልጋህ ላይ ተኝተህ ሳለ በአእምሮህ የነበረው ሕልምና ራእይ ይህ ነው፦

29. “ንጉሥ ሆይ፤ ተኝተህ ሳለ፣ አእምሮህ ወደ ፊት ሊሆን ስላለው ነገር ያሰላስል ነበር፤ ምስጢርን ገላጭ የሆነውም ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር አሳየህ።

ዳንኤል 2