16. በዚህን ጊዜ፣ ዳንኤልም ገብቶ ሕልሙን ይተረጒምለት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።
17. ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ተመልሶ ለጓደኞቹ ለአናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገሩን ገለጠላቸው።
18. እርሱና ጓደኞቹ ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገደሉ፣ የሰማይ አምላክ ምሕረት ያደርግላቸውና ምስጢሩንም ይገልጥላቸው ዘንድ እንዲጸልዩ አሳሰባቸው።
19. ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ፤
20. እንዲህም አለ፤“ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ።
21. ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ደግሞም ያወርዳቸዋል፤ጥበብን ለጠቢባን፣ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።
22. የጠለቀውንና የተሰወረውን ነገር ይገልጣል፤በጨለማ ያለውን ያውቃል፤ብርሃንም ከእርሱ ጋር ይኖራል።
23. የአባቶቼ አምላክ ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ፤አከብርሃለሁም፤ጥበብንና ኀይልን ሰጥተኸኛልና፤ከአንተ የጠየቅነውን ነገር አሳውቀኸኛል፤የንጉሡን ሕልም አሳውቀኸናል።”