ዳንኤል 10:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፣ ብልጣሶር ለተባለው ዳንኤል ራእይ ታየው። መልእክቱ እውነት ነው፤ ስለ ታላቅ ጦርነትም የሚገልጽ ነበረ። መልእክቱንም ይገነዘብ ዘንድ በራእይ ማስተዋል ተሰጠው።

2. በዚያን ጊዜ እኔ ዳንኤል ለሦስት ሳምንት አለቀስሁ፤

3. ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ምርጥ ምግብ አልበላሁም፤ ሥጋም ሆነ የወይን ጠጅ ወደ አፌ አልገባም፤ ቅባትም አልተቀባሁም።

4. በመጀመሪያው ወር በሃያ አራተኛው ቀን፣ በታላቁ በጤግሮስ ወንዝ ዳር ቆሜ፣

5. ቀና ብዬ ስመለከት፣ በፊቴ በፍታ የለበሰና በወገቡም ላይ ምርጥ የወርቅ ቀበቶ የታጠቀ አንድ ሰው አየሁ።

6. አካሉ እንደ ዕንቍ፣ ፊቱ እንደ መብረቅ፣ ዐይኖቹ እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹ እንደ ጋለ ናስ የሚያብረቀርቁ፣ ድምፁም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበር።

7. ራእዩን ያየሁት እኔ ዳንኤል ብቻ ነበርሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩት ሰዎች አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ፍርሀት ስለወደቀባቸው ሸሽተው ተደበቁ።

8. ስለዚህ ይህን ታላቅ ራእይ እያየሁ ብቻዬን ቀረሁ፤ ምንም ጒልበት አልነበረኝም፤ መልኬ እጅጉን ገረጣ፤ ኀይልም አጣሁ።

9. ከዚያም የቃሉን ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ፣ በግምባሬ በምድር ላይ ተደፍቼ በከባድ እንቅልፍ ተዋጥሁ።

ዳንኤል 10