57. ሕያው አብ እንደ ላከኝ፣ እኔም ከእርሱ የተነሣ በሕይወት እንደምኖር፣ የሚበላኝም እንዲሁ ከእኔ የተነሣ በሕይወት ይኖራል።
58. ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በሉ፤ ሞቱም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ግን ለዘላለም ይኖራል።”
59. ይህን የተናገረው በቅፍርናሆም፣ በምኲራብ እያስተማረ ሳለ ነበር።
60. ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ይህን ሲሰሙ፣ “ይህ የሚያስጨንቅ ቃል ነው፤ ማንስ ሊቀበለው ይችላል?” አሉ።
61. ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር ማጒረም ረማቸውን ኢየሱስ በገዛ ራሱ ተረድቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ዕንቅፋት ይሆንባችኋልን?
62. ታዲያ፣ የሰው ልጅ ቀድሞ ወደነበረበት ሲወጣ ብታዩ ምን ልትሉ ነው?
63. መንፈስ ሕይወትን ይሰጣል፤ ሥጋ ግን ምንም አይጠቅምም። እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስም ሕይወትም ነው፤
64. ይሁን እንጂ ከእናንተ የማያምኑ አንዳንዶች አሉ።” ይህም፣ ኢየሱስ እነማን እንዳላመኑና ማን አሳልፎ እንደሚሰጠው ቀድሞውኑ ያውቅ ስለ ነበር ነው።
65. ቀጥሎም፣ “ ‘ከአብ ካልተሰጠው በቀር፣ ማንም ወደ እኔ ሊመጣ አይችልም’ ያልኋችሁ ለዚህ ነው” አለ።
66. ከዚህም በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ከዚያም ወዲያ አልተከተሉትም።
67. ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን፣ “እናንተም ደግሞ መሄድ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
68. ስምዖን ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ጌታ ሆይ፤ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ፤
69. አንተ አንድያ የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆንህ አምነናል፤ ዐውቀናልም።”
70. ኢየሱስም መልሶ፣ “ዐሥራ ሁለታችሁንም የመረጥኋችሁ እኔ አይደለሁምን? ነገር ግን ከእናንተ አንዱ ዲያብሎስ ነው” አላቸው።