ዮሐንስ 6:33-47 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

33. የእግዚአብሔር እንጀራ እርሱ ከሰማይ የሚወርድ፣ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።”

34. እነርሱም፣ “ጌታ፣ እንግዲያውስ ይህን እንጀራ ሁል ጊዜ ስጠን” አሉት።

35. ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔም የሚያምን ፈጽሞ አይጠማም።

36. ነገር ግን እንደ ነገርኋችሁ፣ አይታችሁኝም እንኳ አታምኑም።

37. አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፤ ወደ እኔ የሚመጣውንም ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም፤

38. ከሰማይ የወረድሁት የራሴን ፈቃድ ለማድረግ ሳይሆን፣ የላከኝን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ነውና፤

39. የላከኝም ፈቃድ፣ ከሰጠኝ ሁሉ አንድ እንኳ ሳይጠፋብኝ በመጨረሻው ቀን እንዳስነሣ ነው።

40. የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።”

41. አይሁድም፣ “ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ” በማለቱ ያጒረመርሙበት ጀመር።

42. ደግሞም፣ “ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው፣ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? ታዲያ አሁን እንዴት፣ ‘ከሰማይ ወረድሁ ይላል’” አሉ።

43. ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እርስ በርሳችሁ አታጒረምርሙ፤

44. የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ማንም ወደ እኔ መምጣት አይችልም፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ።

45. በነቢያትም፣ ‘ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ’ ተብሎ ተጽፎአል፤ አብን የሚሰማና ከእርሱም የሚማር ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።

46. ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው በቀር አብን ያየ ማንም የለም፤ አብን ያየው እርሱ ብቻ ነው።

47. እውነት እላችኋለሁ፤ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው።

ዮሐንስ 6