ዮሐንስ 6:17-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በጀልባውም ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም ለመሻገር ተነሡ። ጊዜው መሽቶ ነበር፤ ኢየሱስም ወደ እነርሱ ገና አልመጣም ነበር።

18. ኀይለኛ ነፋስ ይነፍስ ስለ ነበር ባሕሩ ተናወጠ።

19. አምስት ወይም ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል እንደ ቀዘፉ፣ ኢየሱስ በውሃ ላይ እየተራመደ ወደ ጀልባዋ ሲመጣ አይተው ደነገጡ።

20. እርሱ ግን፣ “እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው።

21. እነርሱም እንዲሳፈር ፈለጉ፤ ጀልባዋም ወዲያውኑ ወደሚሄዱበት ዳርቻ ደረሰች።

22. በማግሥቱ በባሕሩ ማዶ የቀሩት ሰዎች በዚያ አንዲት ጀልባ ብቻ እንደ ነበረች ተረዱ፤ ኢየሱስ እንዳልተሳፈረና ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን እንደሄዱም ዐወቁ።

23. ከዚያም በኋላ፣ ሌሎች ጀልባዎች ከጥብር ያዶስ፣ ሕዝቡ ጌታ የባረከውን እንጀራ ወደ በላበት ስፍራ መጡ።

24. ሰዎቹም፣ ኢየሱስ ወይም ደቀ መዛሙርቱ በዚያ አለመኖራቸውን እንዳወቁ፣ ኢየሱስን ፍለጋ በጀልባዎቹ ወደ ቅፍርናሆም ሄዱ።

25. ከባሕሩ ማዶ ባገኙትም ጊዜ፣ “ረቢ፤ መቼ ወደዚህ መጣህ?” አሉት።

26. ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ እንጂ፣ ታምራዊ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።

27. ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ፤ ለዚህም እግዚአብሔር አብ ማረጋገጫ ማኅተሙን በእርሱ ላይ አትሞአልና።”

28. እነርሱም፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ምን ማድረግ አለብን?” አሉት።

29. ኢየሱስም፣ “እርሱ በላከው ታምኑ ዘንድ፣ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው” ሲል መለሰላቸው።

ዮሐንስ 6