2. ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤
3. ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም።
4. ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።
5. እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው።እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።
6. እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው።
7. ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ።
8. ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ።