12. ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም።
13. ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ዓሣውንም ሰጣቸው።
14. እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።
15. በልተው ካበቁ በኋላ፣ ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፣ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፤ ከእነዚህ አብልጠህ ትወደኛለህን?” አለው።እርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም፣ “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።
16. ኢየሱስም ለሁለተኛ ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ በእውነት ትወደኛለህን?” አለው።እርሱም፣ “አዎን፤ ጌታ ሆይ፤ እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም፣ “በጎቼን ጠብቅ” አለው።
17. ሦስተኛም ጊዜ፣ “የዮና ልጅ፣ ስምዖን ሆይ፤ ትወደኛለህን?” አለው።ጴጥሮስም ሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ፣ ‘ትወደኛለህን?’ ብሎ ስለ ጠየቀው ዐዝኖ፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንደምወድህም ታውቃለህ” አለው።ኢየሱስም እንዲህ አለው፤ “በጎቼን መግብ።
18. እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደማትፈልግበት ይወስድሃል።”
19. ኢየሱስ ይህን ያለው ጴጥሮስ በምን ዐይነት ሞት እግዚአብሔርን እንደሚያከብረው ለማመልከት ነው። ከዚህ በኋላም፣ “ተከተለኝ” አለው።
20. ጴጥሮስ ወደ ኋላው ዘወር ሲል፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ሲከተላቸው አየ፤ ይህም ደቀ መዝሙር ያን ጊዜ ራት ሲበሉ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ፣ “ጌታ ሆይ፤ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ያለው ነበር።
21. ጴጥሮስም ባየው ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ እርሱስ?” ብሎ ጠየቀ።
22. ኢየሱስም፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ እንኳ አንተን ምን ቸገረህ? አንተ ራስህ ተከተለኝ” አለው።
23. በዚህ ምክንያት ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ኢየሱስ ግን፣ “እስክመለስ ድረስ በሕይወት እንዲኖር ብፈልግ አንተን ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ እንደማይሞት አልነገረውም።
24. ስለ እነዚህ የሚመሰክረውና ይህን የጻፈው ይኸው ደቀ መዝሙር ነው፤ ምስክርነቱም እውነት እንደሆነ እናውቃለን።
25. ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሁሉም ነገር ቢጻፍ፣ ለተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ ዓለም በቂ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።