11. ኢየሱስም ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ በገሊላ አውራጃ በቃና ከተማ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።
12. ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ።
13. የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።
14. በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ።
15. የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ።
16. ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።
17. ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።
18. አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።
19. ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።
20. አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት።
21. ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር።
22. ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።