ዮሐንስ 19:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው።

12. ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሣር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።

13. ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ ‘የድንጋይ ንጣፍ’ በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ ‘ገበታ’ ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ።

14. ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር።ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው።

15. እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ።ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ።የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት።

16. በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤

17. እርሱም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በአራማይክ ‘ጎልጎታ’ ተብሎ ወደሚጠራው ‘የራስ ቅል’ ወደተባለው ቦታ ወጣ።

18. በዚያም ሰቀሉት፤ ከእርሱም ጋር ሁለት ሰዎች፣ አንዱን በዚህ በኩል፣ ሌላውን በዚያ በኩል፣ ኢየሱስንም በመካከል አድርገው ሰቀሉ።

19. ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ ‘የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ’ የሚል ነበር።

20. ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር።

21. የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት።

22. ጲላጦስም፣ “በቃ፤ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ።

23. ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር።

24. ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣“ልብሴን ተከፋፈሉት፤በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።

25. በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀልዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር።

26. በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤

27. ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።

ዮሐንስ 19