1. ኢየሱስ ይህን ካለ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሆኖ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻገረ፤ ማዶ ወደ ነበረውም የአትክልት ስፍራ ገቡ።
2. ብዙውን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዚያ ስለሚገናኝ፣ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ቦታውን ያውቅ ነበር።
3. ይሁዳም ወታደሮችን እንዲሁም ከካህናት አለቆችና ከፈሪሳውያን የተላኩ ሎሌዎችን እየመራ ወደ አትክልቱ ስፍራ መጣ፤ እነርሱም ችቦ፣ ፋኖስና የጦር መሣሪያ ይዘው ነበር።
4. ኢየሱስም የሚደርስበትን ሁሉ ዐውቆ ወጣና፣ “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው።