ዮሐንስ 13:11-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. “ሁላችሁም ንጹሓን አይደላችሁም” ያለው አሳልፎ የሚሰጠው ማን እንደሆነ ያውቅ ስለ ነበር ነው።

12. እግራቸውን አጥቦ ካበቃ በኋላም፣ ልብሱን ለብሶ ተመልሶ በቦታው ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?

13. እናንተ፣ ‘መምህርና፣ ጌታ’ ትሉኛላችሁ፤ ትክክል ነው፤ እንደምትሉኝ እንዲሁ ነኝና።

14. እንግዲህ እኔ ጌታችሁና መምህራችሁ ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተም እንደዚሁ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል።

15. እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ ምሳሌ ትቼላችኋለሁ።

16. እውነት እላችኋለሁ፤ አገልጋይ ከጌታው፣ መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም።

17. እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ።

18. “ስለ ሁላችሁ መናገሬ አይደለም፤ የመረጥኋቸውን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን፣ ‘እንጀራዬን አብሮኝ የቈረሰ ተረከዙን አነሣብኝ’ የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው።

19. “ሲፈጸም እኔ እንደሆንሁ ታምኑ ዘንድ፣ ይህ ከመሆኑ በፊት አሁን ነገርኋችሁ።

20. እውነት እላችኋለሁ፤ እኔ የላክሁትን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔን የተቀበለም የላከኝን ይቀበላል።”

21. ይህን ካለ በኋላም ኢየሱስ በመንፈሱ ታውኮ፣ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል” ሲል በግልጽ ተናገረ።

22. ደቀ መዛሙርቱም ማንን ማለቱ እንደሆነ ግራ ተጋብተው እርስ በርሳቸው ተያዩ።

23. ከእነርሱ አንዱ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ ተቀምጦ ነበር።

24. ስምዖን ጴጥሮስም ይህን ደቀ መዝሙር በምልክት ጠቅሶ “ማንን ማለቱ እንደሆነ ጠይቀው” አለው።

25. እርሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ደገፍ ብሎ፣ “ጌታ ሆይ፤ ማን ይሆን?” ብሎ ጠየቀው።

26. ኢየሱስም፣ “ይህን ቊራሽ እንጀራ ከወጭቱ አጥቅሼ የምሰጠው እርሱ ነው” አለው፤ ከዚያም ቊራሹን እንጀራ አጥቅሶ ለስምዖን ልጅ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው።

27. ይሁዳም ቊራሹን እንጀራ እንደ ተቀበለ ወዲያው ሰይጣን ገባበት።ኢየሱስም፣ “የምታደርገውን ቶሎ አድርግ” አለው፤

28. ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለምን እንዲህ እንዳለው ማንም አላወቀም ነበረ።

29. ይሁዳ ገንዘብ ያዥ ስለ ነበር፣ አንዳንዶቹ ለበዓሉ የሚያስፈልግ ነገር እንዲገዛ ወይም ለድኾች እንዲሰጥ ኢየሱስ የተናገረው መሰላቸው።

ዮሐንስ 13