3. ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጒቼ ነበር፤ ነገር ግን ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።
4. ከረጅም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኵሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።
5. ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።
6. የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል።