8. “ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብፅ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ።
9. አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ‘ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የመላው ግብፅ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና።
10. ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ።
11. ገና ወደ ፊት የሚመጣ የአምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ ያለበለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’
12. “ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው።
13. በግብፅ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።
14. ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው።
15. የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መጨዋወት ጀመሩ።
16. የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው።
17. ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ።
18. ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’
19. “ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ።
20. ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ”
21. የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው።