ዘፍጥረት 31:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እርሱ፣ ‘ደሞዝህ ዝንጒርጒሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደሞዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤

9. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ።

10. “እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ።

11. የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት።

12. እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤

13. የድንጋይ ሐውልት በማቆም ዘይት ቀብተህ የተሳልህባት የቤቴል አምላክ (ኤል) እኔ ነኝ፤ አሁንም ይህን አገር ፈጥነህ ልቀቅ ወደ ተወለድህበትም ምድር ተመልሰህ ሂድ’ አለኝ።”

14. ራሔልና ልያም እንዲህ ብለው መለሱለት፤ “ከአባታችን ሀብት የምናገኘው ምን ውርስ አለ?

15. እኛን የሚያየን እንደ ባዕድ አይደለምን? ደግሞም እኮ እኛን ሸጦናል፣ የተሸጥንበትንም ዋጋ ራሱ በልቶታል።

16. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የነገረህን ሁሉ አድርግ።”

ዘፍጥረት 31