ዘፍጥረት 3:6-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከእርሷም ጋር ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ።

7. የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ።

8. ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሔዋን ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ።

9. እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው።

10. አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።

11. እግዚአብሔርም፣ (ያህዌ)፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከእርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው።

12. አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋር እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።

13. እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት። እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።

14. እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣“ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉተለይተህ የተረገምህ ሁን፤በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህእየተሳብህ ትሄዳለህ፤ዐፈርም ትበላለህ።

ዘፍጥረት 3