1. እባብ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በእርግጥ እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሎአልን?” አላት።
2. ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤
3. ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሎአል።”
4. እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤
5. ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) እንደምት ሆኑ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ስለሚያውቅ ነው።”