8. እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጒድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በስተቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ።
9. ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች።
10. ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጒድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጒድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ።
11. ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
12. ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው።
13. ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ፣ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው።
14. ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ የሥጋዬ ቊራጭ ነህ” አለው።ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ አብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣
15. ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው።
16. ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር።
17. ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር።
18. ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው።
19. ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው።
20. ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው።