22. ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣
23. “ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት።
24. እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤
25. ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው።
26. ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ፤
27. እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) የተመሰገነ ይሁን።”
28. ልጂቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች።
29. ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጒድጓድ ፈጥኖ ሄደ።
30. እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤
31. እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው።
32. ሰውየው ከላባ ጋር ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለእርሱና አብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው።
33. ለሰውየውም ማዕድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጒዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ።ላባም፣ “እሺ፤ ተናገር” አለው።
34. እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤
35. እግዚአብሔር (ያህዌ) ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል።