1. ቀትር ላይ አብርሃም በመምሬ ትልልቅ ዛፎች አቅራቢያ በምትገኘው ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠለት፤
2. ቀና ብሎም ሲመለከት፣ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ፤ ወዲያውም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ፣ ፈጥኖ ወደ ሰዎቹ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም እጅ ነሣ።
3. አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ፣ ባሪያህን አልፈህ አትሂድ፤
4. ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ እዚህም ከዛፉ ሥር ዐረፍ በሉ።
5. ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ፣ እህል ቀምሳችሁ ትበረቱ ዘንድ ምግብ ላቅርብላችሁና ጒዞአችሁን ትቀጥላላችሁ።”እነርሱም፣ “መልካም፤ እንዳልኸው አድርግ” አሉት።
6. አብርሃም በፍጥነት ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ ገብቶ፣ “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ስልቅ ዱቄት አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት።
7. ከዚያም ወደ መንጋው በጥድፊያ ሄዶ፣ አንድ ፍርጥም ያለ ሥጋው ገር የሆነ ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም ጥጃውን ዐርዶ አዘጋጀው።
8. አብርሃምም እርጎ፣ ወተትና የተዘጋጀውን የጥጃ ሥጋ አቀረበላቸው፤ ሲበሉም ዛፉሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር።
9. እነርሱም አብርሃምን፣ “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” ብለው ጠየቁት።እርሱም፣ “ድንኳን ውስጥ ናት” አላቸው።
10. እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ በእርግጥ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተ ጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር።
11. በዚያን ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜአቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር።
12. ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች።
13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች?
14. ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት በተባለው ጊዜ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።”
15. ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች።እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት።
16. ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቊልቊል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው አብሮአቸው ወጣ።
17. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን?
18. አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በእርሱ ይባረካሉ።