ዘፍጥረት 15:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. “አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።”

4. በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።”

5. ወደ ውጪም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቊጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቊጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው።

6. አብራም እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት።

7. ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔ ነኝ” አለው።

8. አብራምም፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ።

9. እግዚአብሔርም (ያህዌ) “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ አብረህ አቅርብልኝ” አለው።

10. አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ዋኖሷንና ርግቧን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም።

11. አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው።

12. ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት።

ዘፍጥረት 15