1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ (ኤሎሂም) እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።”
2. አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣
3. የእግዚአብሔር (ያህዌ) እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል።
4. ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤልና በግብፅ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ”
5. እግዚአብሔር (ያህዌ) ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።”
6. በማግሥቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ነገሩን ፈጸመው፤ የግብፃውያን እንስሳት በሙሉ አለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም።