ዘፀአት 8:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አባይ በጓጒንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ አልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሃቃዎችህ ይገባሉ።

4. ጓጒንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምቶችህም ሁሉ ይመጡባችኋል።’ ”

5. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኩሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጒንቸሮችም በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።

6. አሮንም በግብፅ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጒንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ።

7. ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብፅ ምድር ላይ ጓጒንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።

8. ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ ጓጒንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ።

9. ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጒንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምቶችህና ለሕዝብህ የምንፀልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቸዋለሁ” አለው።

10. ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው። ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።

11. ጓጒንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምቶችህና ከሕዝብህ ተወግደው በዐባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”

12. ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስላመጣቸው ጓጒንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጮኸ።

13. እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጒንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየአጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ።

14. በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች።

15. ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

16. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው።

17. እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብፅ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው።

18. ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም። ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።

19. አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።

ዘፀአት 8