1. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
2. እነርሱን ለመልቀቅ እምቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጒንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ።
3. አባይ በጓጒንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ አልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሃቃዎችህ ይገባሉ።
4. ጓጒንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምቶችህም ሁሉ ይመጡባችኋል።’ ”
5. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኩሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጒንቸሮችም በግብፅ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።
6. አሮንም በግብፅ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጒንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ።
7. ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብፅ ምድር ላይ ጓጒንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።