ዘፀአት 5:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. የግብፅ ንጉሥም፣ “እናንተ ሙሴና አሮን፤ ለምንድ ነው ሕዝቡን ሥራ የምታስፈቱት! በሉ እናንተም ወደየሥራችሁ ተመለሱ”

5. ፈርዖንም፣ “እነሆ፤ አሁን የምድሪቱ ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፤ እናንተም እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” አለ።

6. በዚያኑ ዕለት ፈርዖን ለባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና ለሕዝቡ አለቆች እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤

7. “ለጡብ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ጭድ ካለበት ቦታ ሄደው ራሳቸው ያምጡ እንጂ ከእንግዲህ እናንተ እንዳታቀርቡላቸው።

8. ሆኖም ቀድሞ በሚያቀርቡት ሸክላ ልክ ሠርተው እንዲያቀርቡ አድርጓቸው። የሥራ ድርሻቸውን አትቀንሱ። ሰነፎች ናቸው፤ ‘ሄደን ለአምላካችን መሥዋዕት እንሠዋ’ የሚሉትም ለዚህ ነው።

9. ለሐሰት ወሬ ስፍራ ሳይሰጡ ተግተው እንዲሠሩ ሥራውን አክብዱባቸው።”

10. ከዚያም የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹና አለቆቹ ወጥተው ለሕዝቡ፦ “ፈርዖን የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእንግዲህ ጭድ አልሰጣችሁም፤

11. ሂዱና የራሳችሁን ጭድ ከየትም ፈልጋችሁ አምጡ፤ የሥራ ድርሻችሁ ግን ከቶ አይቀነስም’ ” አሉ።

12. ስለዚህም ሕዝቡ በጭድ ፈንታ ገለባ ለመሰብሰብ በግብፅ ምድር ሁሉ ተሰማሩ።

13. የባሪያ ተቈጣጣሪዎቹም “በየዕለቱ መሥራት የሚገባችሁ ሥራ ቀድሞ ጭድ ስናቀር ብላችሁ ከምትሠሩት ሥራ ማነስ የለበትም” እያሉ ያጣድፏቸው ነበር።

ዘፀአት 5