16. ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ።
17. እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት፣ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የማደሪያው ድንኳን ተተከለ።
18. ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን በተከለ ጊዜ፣ መቆሚያዎቹን በቦታቸው አኖረ፤ ወጋግራዎቹን አቆመ አግዳሚዎቹን አስገባ፤ ምሰሶዎቹንም ተከለ።
19. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ፣ መደረቢያውንም በድንኳኑ ላይ ዘረጋው።
20. ምስክሩን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አስቀመጠው፤ መሎጊያዎቹንም ከታቦቱ ጋር አያያዛቸው፤ የስርየት መክደኛውንም በላዩ ላይ አደረገው።
21. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው ድንኳን አስገብቶ መከለያ መጋረጃውን ሰቀለ፤ የምስክሩንም ታቦት ጋረደው።
22. ሙሴ ጠረጴዛውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ ከማደሪያው በስተ ሰሜን ከመጋረጃው ውጭ አኖረው፤
23. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘውም ኅብስቱን በላዩ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አኖረ።
24. መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ደቡብ በኩል አኖረው፤
25. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘውም መብራቶቹን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አበራ።
26. ሙሴ የወርቅ መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አኖረው፤
27. እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘውም መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣን አጠነበት።
28. ከዚያም መጋረጃውን በማደሪያው ድንኳን መግቢያ ላይ ሰቀለው።
29. የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንም በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ አኖረው፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘውም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን መሥዋዕት በላዩ ላይ አቀረበ።