15. ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን እንደ ቀባህ ቅባቸው፤ መቀባታቸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለሚቀጥል ክህነት ነው።”
16. ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው አደረገ።
17. እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት፣ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የማደሪያው ድንኳን ተተከለ።
18. ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን በተከለ ጊዜ፣ መቆሚያዎቹን በቦታቸው አኖረ፤ ወጋግራዎቹን አቆመ አግዳሚዎቹን አስገባ፤ ምሰሶዎቹንም ተከለ።
19. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ፣ መደረቢያውንም በድንኳኑ ላይ ዘረጋው።
20. ምስክሩን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አስቀመጠው፤ መሎጊያዎቹንም ከታቦቱ ጋር አያያዛቸው፤ የስርየት መክደኛውንም በላዩ ላይ አደረገው።