1. ለመቅደሱ አገልግሎት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ የተፈተሉ ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ።
2. ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ሠሩት፤
3. ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ይሠራ ዘንድ ወርቁን በስሱ ቀጥቅጠው እንደ ክር ቈራረጡት።
4. ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋር ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።
5. በጥበብ የተፈተለው መታጠቂያ በተመሳሳይ መልክ ሆኖ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከኤፉዱ ጋር አንድ ወጥ የሆነና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር የተሠራ ነበረ።
6. የከበሩ መረግዶችን በወርቅ ፈርጦች በመክፈፍ፣ እንደ ማኅተም የእስራኤልን ልጆች ስሞች ቀረጹባቸው።
7. ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው በኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ላይ ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች አያያዟቸው።
8. የደረት ኪሱንም ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መንገድ ሠሩት፤ እንደ ኤፉዱም ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በቀጭኑም ከተፈተለ በፍታ ሠሩት።