1. ለመቅደሱ አገልግሎት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ የተፈተሉ ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ።
2. ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ሠሩት፤
3. ጥበበኛ ባለ ሙያ እንደሚሠራው በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ይሠራ ዘንድ ወርቁን በስሱ ቀጥቅጠው እንደ ክር ቈራረጡት።
4. ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋር ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።