ዘፀአት 37:5-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. መሎጊያዎቹንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

6. ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ።

7. ከዚያም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤልን ከመክደኛው ጫፎች ላይ ሠራ።

8. አንዱን ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ላይ፣ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ጫፍ ላይ ሠራ፤ ከሁለቱ ጫፎች ላይ ከክዳኑ ጋር አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው፤

9. ኪሩቤልም የስርየት ክዳኑን በመሸፈን ክንፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤል ወደ ስርየት መክደኛው እየተመለከቱ እርስ በርሳቸው ገጽ ለገጽ ነበሩ።

10. ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታውም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሠሩ።

11. ከዚያም በንጹህ ወርቅ በመለበጥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁለት።

12. በዙሪያውም ስፋቱ አንድ ስንዝር የሆነ ጠርዝ በማበጀት በጠርዙ ላይ የወርቅ ክፈፍ አደረጉበት።

13. ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተው አራቱ እግሮች ካሉበት ከአራቱ ማእዘኖች ጋር አያያዟቸው።

14. ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ ከጠርዙ አጠገብ ሆኑ።

15. ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች ከግራር ዕንጨት የተሠሩና በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።

16. የጠረጴዛውን ዕቃዎች ይኸውም ዝርግ ሳሕኖችን፣ ድስቶችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን እንዲሁም የመጠጥ መሥዋዕቱ ማፍሰሻ የሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች ከንጹሕ ወርቅ ሠሯቸው።

ዘፀአት 37